ጥቅምት 2 ቀን 2013
ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ በመስከረም ወር 2013 ዓ/ም በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የሰብአዊ መብት አያያዝ ረገድ የተስተዋሉ ዋና ዋና ክስተቶችን መሰረት በማድረግ ይህንን ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥቶል፡፡
በመተከል ዞን የደረሰ ጥቃት፤
ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ እና ቡለን ወረዳዎች በጳጉሜ ወር 2012 ፣እንዲሁም ዳንጉር ወረዳ በንገዝ ቀበሌ በመስከረም ወር 2013 በታጠቁ ቡድኖች ዘርን መሰረት ባደረጉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጎች እንደተገደሉና እንደቆስሉ፤ ብሎም ንብረታቸው እንዲወድምባቸው ተደርጓል፣ ገሚሶቹም አካባባቢውን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል፡፡ የአይን እማኞች እንደገለፁትና የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃለፊዎች እንዳረጋገጡት በአካባቢው የነበሩ የፀጥታ ሀይል ዜጎቹን የመጠበቅ ግዴታውን ሳይወጣ ቀርቷል፡፡ በመስከረም ወር የደረሰው ጥቃት የፌደራል መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ አካባቢው በመሄድና የፀጥታ ኃይሉን በአካባቢው እንዳሰማራ ከገለፀ በኋላ መሆኑ የችግሩን አሳሳቢነት የሚያሳይ ነው፡፡
በኮንሶ ዞን የተከሰተ ግጭት
በተመሳሳይም በደቡብ ክልል በኮንሶ ዞንና በአሌ ልዪ ወረዳ አዋሳኝ ቀበሌያት በተከሰተ ግጭት የሰው ህይወት መጥፋትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን በግጭቱ ምክንያትም ከ5000 በላይ ነዋሪዎች ከጥቃት በመሸሸ አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን በመስከረም ወር መጀመሪያ ሳምንት ላይ ከተከሰቱ አበይት የሰብአዊ መብት ጥሠቶች አንዱ ነበር፡፡
በጎርፍ አደጋ ህይወታቸው አደጋ ላይ የወደቁ ዜጎች
በሌላ በኩል ከ496ሺ989 በላይ የሚሆኑ ዜጎች በጎርፍ አደጋ ምክንያት በአፋር፣ አማራ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ሱማሌ ክልሎች ውስጥ ለጉዳት ተዳርገዋል።እንዲሁም 134ሺ889 ሰዎች መፈናቀላቸውን፣ በርካታ ቤቶች መፍረሳቸውን፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ህይወት አደጋ ላይ መውደቁ እና ዜጎች በተጠጋጋ ሁኔታ በካምፕ ውስጥ እንዲሰፍሩ በመደረጉ ለኮቪድ ወረርሽኝ በሚያጋልጥ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን በአካባቢው የተንቀሳቀሱ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ስጋታቸውን በመግለጽ መንግስትን አሳስበዋል፡፡
የኃይማኖት ነጻነትን የሚጋፉ እርምጃዎች
የዜጎች የሀይማኖት ነፃነት ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያለው መብት መሆኑ ይታወቀል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ አንዳንድ ዞኖችና ወረዳዎች፣ በደቡብ ክልል በሆሳእና ከተማ የመስቀል በዓል ሀይማኖታዊ መሰረቱን ይዞ እንዳይከበር መሰናክል እንደተፈጠረባቸው አማኞች ገልፀዋል፡፡ በተለይም የኮቪድን በሽታ እንደከልካይ ምክንያት በማድረግ ገደብ መደረጉን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
የፍርድ ቤት ውሳኔን አለማክበር እና የዜጎችን የዋትና መብት መጋፋት
በመሰከረም ወር የተከሰተው ሌላው መሰረታዊ የመብት ጥሰት የፍርድ ቤት ውሳኔን ያለማክበር ሁኔታዎች ናቸው፡፡ በመሰረቱ የዋስትና መብት አላስፈላጊ እስራትን ለማስቀረት ወሳኝ የሆነ መብት ነው፡፡ በተለይም በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ ልደቱ አያሌው ዋስትና በማስያዝ እንዲወጡ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም ተጠርጣሪ ግለሰቡን በዋስትና ለመልቀቅ ፍቃደኛ ያለመሆን ሁኔታዎች ተስተውላል፡፡ የፍርድ ቤት ውሳኔን አለማክበር ለሰብአዊ መብቶች መከበር አደጋ ከመሆኑ በዘለለ እንደሀገር ለተጀመረው የፍትህ ስርአት ለውጥ አደጋ የመፍጠር እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡
የሰዎችን ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነጻነት አደጋ ላይ መጣል
ግለሰቦች ከቦታ ቦታ መዘዋወር ብሎም በሚፈልጉት ቦታ የመኖርና ንብረት ማፍራት በኢፌድሪ ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያለው መብት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ የመሰከረምን ወር ጨምሮ በተለያዩ ግዜያት መንገዶች ሲዘጉ ብሎም ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩ ዜጎች ችግር ሲደርስባቸው ተስተውሏል፡፡ በተለይም ከባህር ዳር ወደ አዲሰ አበባ በሚጓዙ ተጓዦች ላይ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ አንዳንድ ከተሞች የጉዞ መስተጓጎልና ገሚሶቹ መታወቂያቸው እየታየ ወደ ደጀን ከተማ እንዲመለሱ መደረጋቸውን ተጓዦች በአቤቱታ መልክ ለተለያዩ ሚዲያዎች አቅርበዋል፡፡ ይህ ድርጊት ዜጎች በሀገራቸው ያላቸውን የመዘዋወር ነፃነት የሚገድብ ነው፡፡
ምክረ ሃሳቦች
በመሆኑም ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ፤ መንግስት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የመፍትሔ እርምጃዎች እንዲወስድ ጥሪ ያቀርባል፡-
- የፊደራል መንግስትና የቤንሻንጉል ክልል ዘርን መሰረት ያደረጉ ተመሳሳይ ጥቃቶች እንዳይፈፀሙ ለዜጎች ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርጉ፣ የተፈናቀሉ ግለሰቦችን ወደቀያቸው እንዲመለሱ በማድረግ ለተጎዱ ዜጎች ተገቢውን ከሳ እንዲክሱ ፣ በተደጋጋሚ በአካባቢው ጥቃት የሚያደርሱ የታጠቁ ሀይሎች ላይ አስፈላጊ የሆነውን ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ አከባቢውን ከታጣቂ ሀይሎች ነፃ እንዲያወጡ እንዲሁም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በጉዳዩ ላይ ተሳትፎ የነበራቸውን አካላት ወደ ህግ እንዲቀርብ በማድረግ በተሳትፎቸው ልክ በህግ ተጠያቂ እንዲደረጉ፣
- መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለግጭቶች ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን በአግባቡ በመለየት ግጭቶቹ ከመከሰታቸው በፊት የእርምት እርምጃ የሚወሰድበትን ስርአት በመዘርጋት በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰቱ የእርስ በርስ ግጭቶችን ሊያስወግድ ይገባል፡፡
- መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየደረሱ ያሉ የጎርፍ አደጋዎችን አስከፊ አደጋ እንዳያደርሱ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ሊደርስ የሚችለውን የሰብአዊ ቀውስ ሊቀንስ ይገባል፡፡ በተለይም ዜጎች ለኮቪድ እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ እንዳይሆኑ አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎችን ሊያከናውን ይገባል፡፡
- መንግስት በተለያዩ አከባቢዎች ቁጥራቸው አነስተኛ በሆኑ አማኒያን ላይ የሚደርስን ጣልቃ ገብነተም ሆነ ተፅዕኖ ሊከላከል ይገባል፡፡ መሰረታዊ የሆነውን የዜጎች የሀይማኖት ነፃነት የሚገድቡ አካላትን ተጠያቂ የሚያደርግ አሰራር ሊኖር ይገባዋል፡፡ በተለይም የተለያዩ አሳማኝ ያልሆኑ ምክንያቶችን በማንሳት ዜጎች በነፃነት የሚከተሉትን ሃይማኖታዊ ሥርዓት እንዳይተገብሩ መሰናከል በሚፈጥሩ አካላት ላይ ህጋዊ የሆነ እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡
- የፍርድ ቤትን ውሳኔ ማክበር ለሰብአዊ መብቶች መከበር እጅግ ወሳኝ ነገር በመሆኑ በፍርድ ቤት የዋስትና መብት የተፈቀደላቸውና አስፈላጊውን የዋስትና ሁኔታ ያሟሉ ተጠርጣሪዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር ሊፈቱ ይገባል፡፡ በመሆኑም የፍርድ ቤት ውሰኔ እንዳይፈፀም መሰናክል የሚፈጥሩ የመንግስት አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡና ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራርን መንግስት እንዲመሰረት፡፡
- የግለሰቦችን ከቦታ ወደ ቦታ መዘዋወር የሚገድቡ አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እንዲያደርግ፣ ተገቢውን ክትትል በማድረግ የዜጎችን ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ በመገደብ በዜጎች ላይ እንግልትና እንዳይደርስ በአፅኖት እናሳስባለን፡፡