የኢትዮጵያ መንግስት በሳዑዲ አረቢያ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመባቸው የሚገኙ ዜጎቻችንን ወደ ሃገር ለመመለስ በርካታ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጅ አሁንም በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ብዛት ያላቸው ዜጎች ሞት፣ ኢ-ሰብአዊ አያያዝ እንዲሁም ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ለተለያዩ መገናኛ ብዙሀን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ አል አይን አማርኛ ታህሳስ 25 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጣው ዘገባ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች “የእስር ቤት በር የሚከፈትልን ሰው ሲሞት ብቻ ነው” ማለታቸውን እና በአንድ ክፍል ውስጥ እስከ 500 ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መታሰራቸውን ገልጧል፡፡ አል አይን ስደተኞቹን ዋቢ በማድረግ ህፃናት በእስር ቤት እያሉ በበሽታ እና በርሃብ መሞታቸውን፤ ዜጎች ያለ ምግብ፣ ልብስ እና ውሃ እንዲሁም በህመም እየተሰቃዩ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከወራት በፊት ‘ሂውማን ራይትስ ዋች’ የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ከየመን ወደ ሳዑዲ የገቡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በጅምላ ለእስር መዳረጋቸውን መግለፁ አይዘነጋም፡፡ በተመሳሳይ ‘አዲስ ስታንዳርድ’ በነሐሴ 21 ቀን 2013 የሳዑዲ መንግስት የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸውና የሌላቸውን እንዲሁም ምንም አይነት ወንጀል ያልፈፀሙ ኢትዮጵያውያንን ማሰሩን የችግሩ ሰለባ የሆኑ ዜጎችን በማነጋገር ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል እንደ ሂውማን ራይትስ ዋች እና የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ያሉ አለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ተቋማት እና ግብረሰናይ ድርጅቶች የእነዚህን ስደተኞች ጉዳይ በሚመለከት ለሳኡዲ መንግስት ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ እና ጉዳያቸው በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ትኩረት እንዲያገኝ ሲወተውቱ የነበረ ቢሆንም የስደተኞቹ አያያዝ መሻሻል እያሳየ አይደለም፡፡
በመሆኑም መንግስት ከሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ጎን ለጎን ዜጎችን ወደ ሃገራቸው የመመለስ ሂደቱን አጠናክሮ በመቀጠል ዜጎቹን ከሞትና ከስቃይ መታደግን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በተጨማሪም መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች አያያዝ ሰብአዊነትን የተላበሰ እንዲሆን ማድረግን እና እንዲሁም ተመላሽ ዜጎችን የማቋቋሙን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ስንል ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
በመጨረሻም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና የዜና አውታሮች አሰቃቂ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀምባቸው ለሚገኙ ኢትዮጲያዊያን ድምፅ በመሆን የድርሻቸውን እንዲወጡ እንዲሁም የሳዑዲ አረቢያ መንግስት የስደተኞችን እና እስረኞችን መብቶች፤ የተባበሩት መንግስታትን ቻርተር እና አለም አቀፍ ህጎችን እንዲያከብር እንዲወተውቱ ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ ጥሪውን ያቀርባል፡፡