ጋዜጣዊ መግለጫ
ባሳለፍነው ወር በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የሰብአዊ መብት አያያዝ ረገድ የተስተዋሉ ዋና ዋና ክስተቶችን እና የመብት ጥሰቶች ላይ መሰረት በማድረግ ይህንን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ባወጣቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች የዜጎችን ማንነት መሰረት አድርገው በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እየደረሱ ያሉት ጥቃቶች እየተበራከቱ እና እየተባባሱ መሆኑን ገልጿል። በእነዚህ ጥቃቶችም ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ሕዝብ የጥቃት ሰለባ መሆኑን ሌሎች የመብት ተሟጋች ድርጅቶችም በመግለጫዎቻቸው ስጋቶቻቸውንም ጭምት አክለው ሲገልጹ ቆይተዋል። ይህ በእንዲህ እያለ ከሁለት ሳምንታት በፊት በአገሪቱ የሰሜን ክፍል፣ በትግራይ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት የአገሪቱን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ አድርሶታል።
የትግራይ ልዩ ሀይል በክልሉ ውስጥ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ጦር አባላት ላይ በካምፕ ውስጥ እያሉ ያደረሱባቸው አሰቃቂ ጥቃት ለዚህ ጦርነት መቀስቀስ ዋነኛ ምክንያት ቢሆንም በክልሉ መንግስት እና በፌዴራል መንግስቱ መካከል የነበረው መሻከር እና በመግለጫዎች የተደገፈ መናቆሮች ወደ እርስ በርስ ግጭት ሊያመራ እንደሚችል አለም አቀፍ የግጭት አጥኚ አካላት ጭምር ሲያሳስቡ ቆይተዋል። ህውሃት የሚመራው የክልሉ ልዩ ኃይል በመከላከያ አባላት ላይ ከወሰደው ድንገተኛ አሰቃቂ እርምጃ በተጨማሪም በክልሉ ውስጥ ማይካድራ በተባለ ሥፍራ ቁጥራቸው ወደ አምስት መቶ የሚጠጉ ንጹሃን ዜጎችን በጅምላ ተገድለው መገኘታቸውን ከመንግስት እና ከተለያዩ ምንጮች ለማረጋገጥ ተችሏል። ይህ በሰው ዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በሌሎች ስፍራዎችም ቁጥሩ ይለያይ እንጂ ተደጋግሞ እየተፈጸመ መሆኑ ድርጅታችንን ክፉኛ አሳስቦታል።
በትግራይ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሳቢያ ቁጥራቸው በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተፈናቀሉ መሆኑን እና እንደ አንዳንድ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘገባም ከሃያ ሺ በላይ የሚቆጠሩ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ከግጭቱ በመሸሽ ወደ ሱድን እና ሌሎች አጎራባች አገሮች እየተሰደዱ መሆኑ ተገልጿል። በግጭቱ ሳቢያ መንገዶች በመዘጋጋታቸው እና የጸጥታውም ሁኔታ አስጊ በመሆኑ መሰረታዊ የሆኑ እንደ ምግብ እና የጤና አቅርቦቶች በሚፈለገው መጠን ለነዋሪው ሕዝብ ሊደርስ እንዳልቻለ እና በዚህም ሳቢያ የብዙ ሰዎች ሕይወት የከፋ አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ የበጎ አድራጊ ድርጅቶች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
ከጦርነቱ መከሰት ቀደም ብሎም ሆነ በኋላ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች የተፈጸሙ ሲሆን ሲሆን በተለይም፡-
በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራ ፈርዳ ወረዳ በ ጥቅምት 8 እና 9 ማንነታቸው ባልታወቀ አካለት በደረሰ ጥቃት ብዛት ያለቸው ዜጎች ማንነትን መሰረት ባደረገ ጥቃት ህይወታቸውን አጥተዋል፣ አካላቸው ጎድሎል፣ ንብረታቸው ወድሟል፡፡ ከቦታው እየወጡ ባሉት መረጃዎች ከአንድ ቤተሰብ ብቻ 4 እና 5 የቤተሰብ አባላት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፡፡ በዚህ ጥቃት ህፃናት፣ አረጋውያንና ሴቶች ጭምር የጥቃት ሰለባ ሆነዋል፡፡
በተመሳሳይም በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ስር በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ማለትም በምዕራብ ሸዋ ዞን ምዕራብ ወለጋ እና በሆሩ ጉድሩ ዞኖች ማንነታቸው በግልፅ ባልታወቁ አካላት በሚወስዱት እርምጃ የሰላማዊ ሰዎች ህይወት በተደጋጋሚ መጥፋቱ ታውቆል፡፡ በተለይም በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ዲላ ጎጎላ ታንታ ቀበሌ ታጣቂዎች በቀን 22/02 2013 በአካባቢው ኑሮቸውን መስረተው የሚኖሩ የአማራ ብሄር ተወላጅ የአካባቢው ነዋሪዎችን ለስብሰባ ትፈለጋላችሁ በማለት በመጥረት በአሰቃቂ ሁኔታ በደረሰ ጥቃት ቁጥራቸው ከ40-60 ድረስ የሚደርሱ ንፁኃን ዜጎች ህይወታቸውን እንዲያጡ ተደርጎል፡፡ ከዚህ ባለፈም ብዛት ያለቸው የአማራ ብሄር ተወላጆች በዚሁ ጥቃት ለአካል መጉደል መዳረጋቸው ተውቋል፡፡ ጥቃቱ የተፈፀመው በአካባቢው ለጥበቃ የተሰማራው የመከላከያ ሰራዊት አካባቢውን ለቅቆ በወጣበት ቀን መሆኑ በአካባቢው የነበረውን ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ያመላክታል፡፡ ከጥቃቱ በሓላ በአካባቢው የሚኖሩ የአማራ ብሄር ተወላጅ ዜጎች አሁንም ቢሆን የደህንነት ስጋት ያለባቸው መሆኑን በተደጋጋሚ ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ገልፀዋል፡፡
በአፋርና በሱማሌ ክልል አጎራባች አካባቢዎች በተነሳ ግጭት ብዛት ያለቸው ዜጎችን ለሞትና ለአካል ጉዳትና እንዲሁም መፈናቀል ዳርጎል፡፡ በተለይም በዚህ አካባቢ ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ በሚነሳ ግጭት የብዙዎችን ህይወት አያጠፋ መሆኑ ይተወሳል፡፡
ከዘህ ባሻገርም ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው መንገድ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በምሽት ሰአት ተጓዦች ላይ እና በአሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ደርሶል በአንዳንድ አሽከርካሪዎች ላይም የአካል መጉደልና የህይወት መጥፋት አስከትሏል፡፡
የመሰብሰብ ነፃነትና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት መሰረታዊ የሰብአዊ መብትና በኢፊድሪ ህገመንግስትም በአንቀፅ 30 እውቅና የተሰጠው መሆኑ ይታወቀል፡፡ በጥቅምት ወር አብን የሚሰኘው ፓሪቲ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንዲወገዝ ለማድረግ የጠራው ሰልፍ እንዳይደረግ ተክልክሎል፡፡
በመሆኑም ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ፤ መንግስት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የመፍትሔ እርምጃዎች እንዲወስድ ጥሪ ያቀርባል፡-
- በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት በአፋጣኝ እንዲገታ እና ለንጹሃን ዜጎች ሞትም ሆነ በመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ጥቃት ያደረሱ እና ትዕዛዝ የሰጡ ሰዎች በቍጥጥር ስር ውለው ለፍርድ እንዲቀርቡ፤
- በትግራይ ክልል ከጦርነቱ በመሸሽ ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ እና ወደ ጎረቤት አገር የተሰደዱ ዜጎች በቂ ድጋፍ እና ጥበቃ እንዲደረግላቸው፤ እንዲሁም በክልሉ ውስጥ የሚገኙ እና በመሰረታዊ አቅርቦት እጥረት ህይወታቸው ለአደጋ የተጋለጡ ዜጎች የሰብአዊ እርዳታ በተፋጠነ ሁኔታ እንዲደርሳቸው ሁኔታዎች እንዲመቻቹ፤
- የፊደራል መንግስትና የኦሮሚያ ክልል ዘርን መሰረት ያደረጉ ተመሳሳይ ጥቃቶች እንዳይፈፀሙ ለዜጎች ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግ፣ የተፈናቀሉ ግለሰቦችን ወደቀያቸው እንዲመለሱ በማድረግ ለተጎዱ ዜጎች ተገቢውን ከሳ እንዲክሱ ማድረግ፣ ከዚህ ባሻገር ዘርን መሰረት በማድረግ በየአካባቢው በሚደረጉ ጥቃቶች ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳትፎ ያላቸው አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ በተሳትፎቸው ልክ በህግ ተጠያቂ እንዲደረጉ፣
- ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንዳሳሰብነው መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለግጭቶች ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን በአግባቡ በመለየት ግጭቶቹ ከመከሰታቸው በፊት የክትትል ስርአት በመዘርጋትና የእርምት እርምጃ በማዘጋጀት በሀገሪቱ በተለያዩ ግዜያት የሚከሰቱ የእርስ በርስ ግጭቶችን ሊያስወግድ ይገባል፡፡
- በሱማሌና አፋር ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እንዲሁም በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ከማንነትና ከቦታ ይገባኛል ጥያቄ ጋር ተያይዞ በሚነሱ ጥቃቶች የሚደርሱ ግጭቶችን ለማስቀረት መንግስት የክልል መንግስታትንና ህዝቡን ያሳተፈ ሁሉን አቀፍ መፍትሔ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡
- የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት በኢፊዲሪ ህገመንግሰት እውቅና የተሰጠውና በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ድጋፍ ያለው መብት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተለያዩ ምክንቶች መሰረት በማድረግ ይህንን መብት መገደቡ ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰናክል በመሆኑ መንግስት የተለያዩ ሰንካላ ምክንያቶችን እያነሳ ቡድኖች የሚጠይቁትን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን ሊገድብ አይገባም፡፡