አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ73ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡ ሰብአዊ መብቶችን ማክበር በእለት ተእለት እንቅስቃሴአችንና ባህሪያችን ሊተገበር የሚገባው ቢሆንም ቀኑ በአለም አቀፍ ደረጃ መዘከሩ ሰብአዊ መብቶችን ማክበር የአለም ህዝቦች ሁሉ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክኒያት የተለያዩ መጠነ ሰፊ የሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተፈፀሙ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቢሮ ከኢትዮጲያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመተባበር  ምርመራ በማድረግ የደረሰውን ጉዳት መጠን እና አይነት በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫዎች ማስቀመጣቸው ይታወሳል፡፡ በመሆኑም  እነዚህ አካላት ላደረጉት ጥረት ያለንን  ከፍተኛ አድናቆት በድርጅታችን ስም  እየገለጽን ወደፊትም እንዲህ አይነቱ ተግባር ሊበረታታ ይገባል  እንላለን፡፡ 

ነገር ግን አሁንም ድረስ እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት ምክንያት በተለይም የህውሃት ሃይሎች ተቆጣጥረዋቸው በነበሩት የአማራ እና አፋር ከልሎች አሰቃቂ እና መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን የሚያረጋግጡ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር በእነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ የመንግስት እና የግል ንብረቶች እና መሰረተ ልማቶች ውድመት እና ዝርፊያ ተፈፅሟል፡፡ የሚመለከታቸው አካላትም የወደሙ እና የተዘረፉትን መሰረተ ልማቶች በማደስ እና በማሟላት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ እንዲሁም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ 

ነገር ግን ከእነዚህ መልሶ የማቋቋም ስራዎች ጎን ለጎን የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በሚገባ የማጣራት፣ ማስረጃዎችን የማሰባሰብ እና ወንጀለኞችን ለፍትህ የማቅረብ ስራዎች ተገቢው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በተጨማሪም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሰለባ የሆኑ ዜጎች በተለይም አስገድዶ መድፈር የተፈጸመባቸው ሴቶች እና ህፃናት የሚያስፈልጋቸውን እገዛ እና ድጋፍ ማድረግ ከፍተኛ ትኩረትን እና የሁሉንም ባለድርሻ አካላት እርብርብ ይሻል፡፡ 

በመሆኑም ሁሉም የሚመለከታቸው መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጦርነቱ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በማጋለጥን፣ መሰነድን እና ወንጀለኞችን ለፍትህ ማቅረብን ብሎም ተጎጂዎችን መርዳትን ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡትና በተግባር የተደገፉ እርምጃዎችንም በአፋጣኝ እንዲተገብሩ ድርጅታችን ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጲያ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ ድርጅታችንም እንደ አንድ አገር በቀል የሰብአዊ መብት ድርጅት በጥሰቶቹ ዙሪያ ምርምር በማካሄድና መረጃዎችንም በማሰባሰብ ረገድ ያለበት የአቅም ውሱንነት እንደተጠበቀ ሆኖ የድርሻውን ሊወጣ ዝግጁ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን። 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *